ሶስተኛው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ልዩ ልዩ ሻምፒዮና፣ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ፍፃሜውን አገኘ። በክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አዘጋጅነት በወልቂጤ ከተማ ለአስር ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የሰነበተው ሶስተኛው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ልዩ ልዩ ሻምፒዮና፣ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።
በአጠቃላይ ውድድሩ የጉራጌ ዞን፣ የሀዲያ ዞን እና የስልጤ ዞን በቀደም ተከተል ከ1 እስከ 3 በመውጣት አጠናቀዋል። ውድድሩ ፍፃሜውን ባገኘበት በዛሬው እለት የጉራጌ ዞን የእግር ኳስ ክለብ ከጠምባሮ ልዩ ወረዳ እግር ኳስ ክለብ ጋር ለዋንጫ የተጫወቱ ሲሆን፣ ጫወታው 90 ደቂቃ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ይህንኑ ተከትሎ በተደረገ የመለያ ምት የጉራጌ ዞን 2 ለ1 ጠምባሮ ልዩ ወረዳን በማሸነፍ ዋንጫውን ማንሳት ችሏል።
በሴቶች እግር ኳስ ደግሞ የሀዲያ ዞን የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ዋንጫ ወስዷል። በፍፃሜው መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ እንደተናገሩት ፌስቲቫሉ የህዝቦች ማንነትና ስፖርታዊ ጨዋነት የታየበት ነው። ወንድማማችነት እና እህታማማችንት ጎልቶ የታየበት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፣ ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አመላክተዋል።
በባህላዊ ስፖርቶች ውድድርም አባቶች ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩልንን በወጣቱ ጥንካሬ ሲንፀባረቅ ታይቷል ብለዋል። በውድድሮቹ ክልሉን የሚወክሉ ተተኪ ወጣት ስፖርተኞች የተገኙበት ስለመሆኑም ተናግረዋል። መርሃ ግብሩ ክልሉ የሰላም ተምሳሌት መሆኑ የታየበት ነው ያሉት አቶ ጌታቸው ውድድሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ አካላት ምስጋና አቅርበዋል። የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ውድድሩ በሰላም መጠናቀቁን ተናግረው፣ ለዚህ ስኬታ ጉልህ ድርሻቸውን የተወጡት የፀጥታ አካላትን አመስግነዋል። በወልቂጤ ከተማ በተካሄደው የዘንድሮው ልዩ ልዩ ሻንፒዮና፣ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ስኬታማ ቆይታ ማድረጋቸውን ተሳታፊዎች ገልፀዋል።
በውድድሩ የእርስ በርስ ትስስር የተጠናከረበትና የአብሮነት ዕሴት የጉበት ነው ብለዋል። የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎችና አመራሮች ላደረጉላቸው መልካም አቀባበልና በቆይታቸውን ላሳይዋቸው ፍቅር እና እንክብካቤ ተሳታፊዎቹ አመስግነዋል። በዕለቱ የዋንጫና የሰርቲፊኬት ሽልማት ስነ ስርዓት ተካሂዶ የመዝጊያ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።