Skip to main content
youth11

የወጣቶችን በራስ መተማመን እና ምክንያታዊ የህይወት ክህሎት ለማጎልበት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ። (ዱራሜ፣ ሚያዝያ 28/2018 ዓ/ም) ቢሮው ከUNFPA አጋር ድርጅት ጋር በመተባበር በሚያከናውነው የወጣቶች ልማት ፕሮግራም ቅንጅታዊ አሠራር ለማጠናከርና በቀሪ ወራት ዕቅድ ላይ ለመምከር ያዘጋጀው መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል። የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌልሾ እንዳስታወቁት ቢሮው የወጣቶች ስብዕና ግንባታ ላይ ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው። 

በፕሮግራሙ ማዕቀፍ የወጣቶች በራስ መተማመን እንዲሁም ምክንያታዊ ወሳኔና የአኗኗር ዘይቤ የመሳሰሉ የህይወት ክህሎቶችን ለማጎልበትና ለውጥ ፈላጊነታቸውን መሠረት ያደረገ የሀገር ፍቅር አቅማቸውን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል። በፕሮግራሙ ድጋፍ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች መዘጋጀታቸውን የገለጹት አቶ ጌታቸው የወጣቶች ስብዕና ማዕከላትን በቴክኖሎጂ ግብዓቶች በማሟላት መንግስት ለዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መሆን ባስቀመጠው ትልም ወጣቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። የፕሮግራሙን ድጋፍ እንደመነሻ በመጠቀም የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ መፈጸም ይገባል ያሉት የቢሮ ኃላፊው ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጀትን ለታለመለት አላማ እንዲያውሉ አሳስበዋል። 

የቢሮው ምክትልና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አሊ በበኩላቸው መንግስት የወጣቱን ሁለንተናዊ ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸው በዚህም ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል። ወጣቱ ካለው ከፍተኛ ቁጥር አንጻር የሚፈጠረውን ሰፊ ፍላጎት በመንግሥት መዋቅር ብቻ ማሟላት ስለማይቻል ቢሮው ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በዕቅድ እየሠራ ነው ብለዋል። የUNFPA ፕሮግራም በክልሉ የተጋላጭ ወጣቶችን ችግር በመፍታትና ለአፍላ ወጣቶች የህይወት ክህሎት ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አቶ ሱልጣን ተናግረዋል። የፕሮግራሙን ድጋፍ ከወጣቶች ፖሊሲ ጋር በማጣጣም መጠቀም ይገባል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ቀሪ ተግባራት በታቀደላቸው ጊዜ እንዲፈጸሙ አሳስበዋል። 

የመድረኩ ተሳታፊዎች የUNFPA ፕሮግራም ለወጣቶች ሁለንተናዊ ስብዕና ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል የበጀት ዓመቱን ቀሪ ተግባራት በቅንጅት ለመፈጸም እንደሚረባረቡም አመላክተዋል። በመርሃግብሩ የክልል፣ የዞንና የልዩ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የባህል ሽማግሌዎች፣ የወጣት ማህበራት ተወካዮች፣ ተገኝተዋል።