Skip to main content
youth14

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ለሀላባ ከተማ እግርኳስ ክለብ የዘመናዊ አውቶቡስ ስጦታ አበረከተ (ሆሳዕና፣ግንቦት 4/2018 )የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ለሀላባ ከተማ እግር ኳስ ቡድን አባላት በቤተ መንግስት አቀባበል አድርገውላቸዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ከረጅም ትጋት በኋላ ለውጤት መብቃት መታደል ነው ብለዋል። ክለቡ ያስመዘገበውን የላቀ ድል ምክንያት በማድረግ የክልሉ መንግስት ለሀላባ እግር ኳስ ቡድን የዘመናዊ አውቶቢስ ሽልማት እንደሚያበረክት ርዕሰ መስተዳድሩ ቃል ገብተዋል። ከአውቶቡስ ሽልማት በተጨማሪ ክለቡ ከሚያስመዘግበው ውጤት በኋላ ተጨማሪ ስጦታ ይበረከትለታል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል። የክለቡ አባላት ባላቸው የላቀ ጥረት ጥቂት ክለቦች ብቻ የሚያገኙትን እድል በላባቸው ማሳካት በመቻላቸው ርዕሰ መስተዳድሩ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል። የቡድኑ አባላት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በሚኖረው ጨዋታ በጥብቅ ዲሲፕሊን ፣ራስን በቡድንም ሆነ በግል ማብቃት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል። መንግስት እና ፓርቲ ለስፖርት ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥተዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በርካታ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል። ክለቡ አሁን ያለውን አቅም ይበልጥ በማጎልበት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨማሪ አቅም መፍጠር እንደሚያስችለውም ርዕሰ መስተዳድሩ ያላቸውን ጽኑ አቋም ገልጸዋል። በእግር ኳስ ጨዋታ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የቡድን ስራ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ቡድኑ ከብዙ ክለቦች ተወዳዳሪ በመሆን ለስኬት መብቃቱን በአብነት ጠቅሰዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ክለቡ ያስመዘገበው ውጤት የሀላባ ብቻ ሳይሆን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ድል በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ በበኩላቸው ክለቡ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ በማለፍ ከ25 ዓመታት ጥረት በኋላ ለውጤት መብቃቱን አድንቀዋል። የተገኘው ድል የጽናት፣የአንድነት እና የትጋት ውጤት መሆኑን ነው አቶ ጌታቸው የገለጹት። በውድድር ዘመኑ የነበረው ብቃት፣በሜዳ ላይ ያሳየው ተጋድሎ የሁላችንም ኩራት ነው ሲሉም አክለዋል። የክልሉ መንግስት ለስፖርት ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት በክልል ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንዳስቻለም ጠቁመዋል።